ሰሙነ ሕማማት “ወአንትሙሰ ተዐቀቡ ወግበሩ ተዝካረ ሕማማቲሁ” የሚለውን የአበውን ትዕዛዝ አብነት በማድረግ የክርስቶስን ሕማም የሚዘከርበት በዓል ነው፡፡ በኦርቶዶክሳውያን ዘንድ ታላቅ ቦታ ያለው እጅግ ልዩ የሆነ ድባብ የሚፈጥር ሊቁ ዪሐንስ አፈወርቅ “ይትባረክ እግዚአብሔር ዘሰመየ ሕማማተ ወልዱ ክቡረ ወስብሐተ”ያለለት በሕማም እና ድካም በአልፎ በታላቅ ፍስሐ እና ሐሴት የሚደመደም በዓል ነው ፡፡ስንዱዋ እመቤትም ይህንን በዓል መሰረት አድርጋ ወንጌልን ገልጣ፣ ስለዚህ ሰማያዊ ምስጢር ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የጥል ግርግዳን እንዳፈረሰ ፣ በደሙ ፈሳሽነነት የሰውን ልጅ እንደታደገው ታስተምራለች፡፡ትላንት፣ ጥንት ፣ ከሁለት ሺሕ አመታት በፊት ሳይሆን ዮም ተሰቅለ፤ ዮም ተንስኣ፤ እያለች፡፡ኢየሱስም ያደረገው ብዙ ሌላ ነገር ደግሞ አለ፤ ሁሉ በእያንዳንዱ ቢጻፍ ለተጻፉት መጻሕፍት ዓለም ራሱ ባልበቃቸውም ነበር እንዳለ ወንጌላዊው ተነግሮ አያልቅም፡፡እኔ ግን ሁሌም በዚህ ሰሞን እጅግ የሚገርመኝ የሊቃውንቱ የተመስጦ ማጠንጠኛ የሆነችው በጦማራችን መጀመሪያ ላይ ያለችው ሐረግ ናት፡፡
በምሴተ ሐሙስ ሊቃውንቱ በታላቅ ተመስጦ ሆነው ደጋግመው ይሉታል፡፡የኔ ቢጤ ጨዋ እንኳ በቀላሉ ቃላቶቹን ይለያቸዋል፡፡ዜማው ልብን ሰርስሮ ሲገባ፣ ጠና ያሉ አባቶች ከእንባቸው ጋር እየታገሉ ፣ ሳግ እየቀላቀሉ ሲያሄዱት እንዴት አንጀት ያኝካል መሰላችኹ፡፡ ሊቀ መዘምር ይልማ ኀይሉ “ኢየሱስም አለ” በተሰኘችው የመንፈስ ፍሬው ዜማውን ከነመልዕክቱ ለማድረስ ያደረገው ጥረት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡
ወደ መልዕክቱ እንግባ፡፡ያው እንደሚታወቀው ለኛ ለኢትዮጵያውያን ጭቆና አዲስ ነገር አይደለም ታላቅ ወንድም ይጨቁነናል ፤ ወላጅ ይጨቁነናል፤የክፍል አለቃ ይጨቁነናል፤ መምህር ይጨቁነናል፤ የሰፈር ጉልቤ ይጨቁነናል፤የቀበሌ ሹም ይጨቁነናል፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ይጨቁነናል… የሚገርመው ብዙዎቻችን ይህንን እንደ ኮሶ የተጣባንን መጨቋቆን ስንቃወም እንታያለን፡፡ ነገር ግን የጩኸታችን ምክንያት እኛ ከላይ ባለመሆናችን ብቻ ነው ፡፡
ታዲያ ለዚህ ህዝብ ነው ከበድ ያለ መልዕክት የደረሰው “እግረ አርዳኢሁ ሐፀበ” የረድ አገልጋይን እግር ማጠብ እንኳን እኛ ለሐዋርያው ጴጥሮስ እጅግ እንደከበደች መጽሐፍ እንዲህ ብሎ ይነግረናል፡፡ “ከእራት ተነሣ ልብሱንም አኖረ፥ ማበሻም ጨርቅ ወስዶ ታጠቀ፤በኋላም በመታጠቢያው ውኃ ጨመረ፥ የደቀ መዛሙርቱንም እግር ሊያጥብና በታጠቀበትም ማበሻ ጨርቅ ሊያብስ ጀመረ።ወደ ስምዖን ጴጥሮስም መጣ፤ እርሱም፦ ጌታ ሆይ፥ አንተ የእኔን እግር ታጥባለህን? አለው።”ይህ ነው ሊቃውንቱን ያነሆለላቸው፤ ነፋሳቸውን ሰቅዞ የያዘው፡፡ ምክንያቱም አይሁድ በዚያን ጊዜ እንደኛ ህዝብ በቀቢጸ ተስፋ የተያዙ ፣ የቄሳሮች የጭቆና ቀንበር ያደቀቃቸው ፣ ማኀበራዊ ቀውስ የነገሰባቸው ነበሩ ልክ እንደኛ፡፡
ቅዱስ ጴጥሮስ የከበደው የአምላኩ የመምህሩ ጎንበስ ብሎ እግር ማጠብ ብቻ አይደለም(እርግጥ እርሱም ታላቅ ምስጢር ነው) የነበረው ስርዓት ደንብ መፍረሱም እንጂ፡፡ ገዥ እና ተገዥ ፣ አለቃ እና ምንዝር ፣ ሕዝብ ና መንግስት ባሪያና አሳዳሪ የሚለውን ስርዓት ማፍረሱ ነው፡፡ለዚሀም ነው ሊቃውንቱ ደግመው ደጋግመው የሚጮሁት ፤ ከባዱን ነገር ነገር ለማፍረስ እራስን ዝቅ ማድረግ ፤ እውነት ነው! ለዚህ አንክሮ ይገባል ፡፡የማይሆነው ሲሆን አንክሮ ይገባል፡፡ ለዚህም ጌታችን እንዲያስተውሉት በአጽንኦት የነገራቸው፡፡ “…ያደረግሁላችሁን ታስተውላላችሁን?…”አንትሙኒ ከመዝ ግበሩ፡፡ለቢጽክሙ፡፡ለወንድሞቻችሁ እንዲሁ አድርጉ እኔ እንደእናትም እንደ አባትም እንደሆንኩላችሁ እናንተም ለወንድሞቻችሁ እንዲሁ እድርጉ፡፡ልብን ጭልጥ አድርጎ የሚያነጉድ፡፡ ሐዋሪያቲሁ ክበበ….