Log out from ‘fazebook’ but log in to facebook
በቅርቡ አምስተኛ አመቷን ባከበረችው በአዲስ ጉዳይ(ሮዝ) መጽሔት ሁለት ተከታታይ እትሞች “ፌስቡክ ከወሲብ ገበያ እስከ አብዮት” የሚል ረጅም ጽሑፍ አነበብኩኝ:: ጽሁፉ እና እኔ የማውቀው ፌስቡክ አልተገናኝቶም ሆኑብኝ፡፡ ከዚያም ለዚህ ፌስቡክን የማያውቅ ፌስቡካዊ ጽሑፍ ምላሽ የምትሆን አጭር መጣጥፍ ለመጣፍም ዳዳኝ፡፡ የመጀመሪያው በርዕሱ ስለጠቀሰው አብዮት እዚህ ግባ የሚባል ዳሰሳ አልቀረበም፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ፌስቡክ አመጣሽ ችግር መከላከያው ምን አንደሆነ አልጠቆመንም ወይንም ፌስቡክን እንዴት ባግባቡ መጠቀም እንዳለብን ምከር ቢጤም የለውም፡፡
በአንድ መንግስታዊ ድርጅት ከሚሰራ ወዳጄ ጋር በዚህ እና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ስንጨዋወት በመስሪያ ቤቱ ያለበትን ብሶት አጫወተኝ፡፡ እንደ እርሱ አለቆች ግንዛቤ ፌስቡክ መጠቀም የዋልጌዎች ስራ ነው፡፡ በስራው ወዳድነቱ እና በጥሩ ስነ ምግባሩ የሚወዱት አለቆች ሳይቀር ፌስቡክ ገጹ ላይ ተስጥቶ አግኝተውት “አንተም ተበላሸህ?” በማለት እንዳዘኑበት ገልጾልኛል፡፡ ይህ የወዳጄ ሮሮ እንዲሁም የአዲስ ጉዳይ መጽሔት ዘገባ የአቻዎቼን የፌስቡክ ውሎ እንድመረምር አስገደደኝ፡፡ እንዲህም ሆኖ አገኘሁት፡፡
ብዙዎቻችን ማለት ይቻላል ጊዜያችንን የምናጠፋው የቆነጃጅትን ፎቶዎች በማየት ነው፡፡ ከዚያም ልጅት ከፈቀደች add በማድረግ፣ እዚህ ግባ የማይባል የእንቶ ፈንቶ chat በማድረግ ነው ፤ በአጠቃላይ digital ድድ ማስጫ አድርገነዋል፡፡ሴት እህቶቻችንም ልዩ ክስተቶችን ቀርጾ ከማሰቀመጥ በዘለለ ለገበያ እንደቀረበ ሸቀጥ ወይንም FBI እንደያዘው ተጠርጣሪ ከተለያየ ማዕዘን በመነሳት የፌዝቡከሮችን ቀልብ ለመሳብ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ወግ አጥባቂ አለቆቻችን ቀርቶ ሌላው በጎ አሳቢ ሊቀላቀለን ፍቃደኛ አልሆነም፡፡የአለቃና ምንዝር ግንኙነትን ለጊዜው ወደጎን ተወት አድርገነው ፊደል ቀመስ ወላጆቻችን እንኳን ይህንን ጉዳይ በበጎ ይመለከቱታል ለማለት ይከብዳል፡፡የተለመደው በቤት ያለ አልበም እንኳን አቧራው የሚራገፈው ቆየት ያለ ወዳጅችንን ቤት ለእንግዳ ያልን እንደሆነ ነው፡፡ፌስቡካዊው ወዳጄ ታምራት ታም ራት ይህንን ወለፈንድ የሚገልጽ አጭር እንካ ሰላንቲያ(chat) ፌስቡክ ግርግዳው ላይ ለጥፎ ሁላችንንም የምር ጥርሳችንን አስከፍቶናል፡፡ በሞቴ ሳቄን ላካፍላችኹ ቢያንስ ፈገግ እንኳ በሉልኝ፡፡
Bety: Weyeeeeeee sitamri eko
Titi: ♥♥♥ tnx kanchi balbeltim ♥♥♥
Bety: eeeeeeeee mozaza lol
Titi ♥♥lol♥♥
Bety: bettam Qonjo nesh Eshi?
Titi: lol thanks lol ahun wede bet lihed new lol
Abebe: Lol
Bety: bye ♥♥♥ lol
ይህን ነገር የሚጋሩት ቴክኖሎጂውን በሩቁ የሚመልከቱት ብቻ አይደሉም፡፡እኛን ፌስቡካወያንን ተቀላቅለው ያቀማቸውን አስተዉለው በዋዛ ፈዛዛ ጊዜያችንን ከምናሳልፍ በማለት ገጻቸውን deactivated አድርገው የፈረጠጡም ይገኙበታል፡፡የፌስቡክ አትጠቀም እጠቀማለው እሰጥ አገባ መነሻም ከዚህ ይመነጫል፡፡ ወዳጆቻችን በፌስቡክ ስንባዝን እንጂ ስንጠቀም አላገኙንም ፡፡ የማርክ ዙከርበርግን ፌስቡክ አያወቁትም፡፡ፌስቡክ ያለው ሌላ እኛ የምንጠቀመው ሌላ፡፡ አንዳንድ ሞያዎች ባለሙያ ነን የሚሉ ሰዎች ሀገሪቱን አጨናንቀዋት እያለ ሙያው ወደሀገራችን አልገባም እንደሚባለው ፌስቡክንም መጠቀም የጀመረን አልመሰለኝም ፡፡
እንደኔ እንደኔ እኛ እየተጠቀምን ያለነው ፌስቡክ ሳይሆን ፌዝቡክን ነው፡፡ከባሪያይቱ አንዱም ከጨዋይቱ ደግሞ ሌላ በድምሩ ሁለት ልጆች ለአብርሃም እንደ ነበሩት በታላቁ መጽሐፍ እንደተጣፈ ለማርክዙከርበርግ ሁለት ልጆች አሉት ፌስቡክ የጨዋይቱ ፤ ፈዝቡክ የባሪያይቱ፡፡ ፌስቡካውያን የጠፋ ወዳጅ ፣ ዘመድ ይፈልጉበታል፤ ከእነርሱ የበለጠ የሀሳብ ልዕልና ያላቸውን ሰዎች ፈልገው ያወጉበታል፡፡በሌሎች መካነ ድር ያገኙትን የማረካቸውን ለወዳጆቻቸው ያካፍሉበታል ፡፡የፈዝቡክ ተጠቃሚዎች ደግሞ በተቃራኒው እራሳቸውን በስም እና በምስል ደብቀው የጽንፍ ቦለቲካቸውን ያራምዳሉ ወይንም መረን በለቀቀ ብልግናቸው የንጹሓንን የፌስቡክ ገጽ ያቆሽሻሉ፡፡
እንግሊዘኛ እና ህልም እንደ ፈቺው ነው ብለን በስልታዊ መላ አለማወቃችንን ብንሸፍንም ጭራ ከሆንባቸው ጉዳዮች አንዱ እንግሊዘኛ ቋንቋን አቀላጥፎ መናገር ነው:: እንግሊዘኛ ቋንቋ በታላቋ ብሪታኒያ ተወልደ፤ በአሜሪካ አደገ፤ ህንድ ታመመ፤ አፍሪካ (አትዮጵያ) ሲደርስ ሞተ የሚል መነሻው የማን እንደሆነ ለጊዜው ያልደረስኩበት አባባል አለ፡፡ እንግሊዘኛ ማወቅ የምሑርነት ምልከት ነው እያልኩ እንዳልሆነ ተረዱልኝ፡፡ነገር ግን በኔ በጥናት ያልተደገፈ ንቁ ተመልካች(active audience) በመሆን ብቻ በተወሰደ ግምት ከእንግሊዘኛ ይልቅ ፌስቡክን በመግደል የሚያሰከስሰን ይመስለኛል፡፡ ለምን ብትሉኝ ከፈርጀ ብዙ ጥቅሞቹ መቋደስን ትተን በአልባሌው ላይ ማተኮራችን ነው፡፡ በንቃተ ህሊና ከብዙዎቹ የአለማችን ህዝቦች አንድ ጋት የራቁ ናቸው ተብለው የሚታሙት አረቦች እንኳ በአግባቡ ተጠቅመውበት የሰው ልጆች ከጭቆና እና ጨቋኞች ጋር የሚያደርገውን የማያልቀውን ትግል ብዙ የስኬት ምዕራፍ እንዲጓዝ አስችለውታል፡፡ታዲያ እኛስ እንደ ፈርኦኖች ሀገር ሰዎች ባይሆን እንኳ በመጠኑ መግባባታችንን የሚጨምር ረብ ያለው ነገር መከወን ሊያቅተን አይገባም፡፡ ሁሉም ነገር በመላ ካልተያዘ ከጥቅሞቹ ጋር ጉዳቶችን ትቶልን ይሄዳል፡፡የእናቶቻችን ቡና ጠጡ እንኳ ለሐሜት ይጋለጣል፡፡ለዚህም ነው አሳን መብላት በብልሃት የምንለው፤ ነገር ግን ፌስቡከ ላይ ይህ ብላሃታችን አልታየም፡፡ ከጨዋይቱ ይልቅ ባርያይቱን ልጅ መምረጣችን የዘመኑን ጥበብ ባግባቡ እንዳንጠቀም አድርጎናል፡፡
ይህንን ክፍተት የሚሞሉ “የሀገር ሰዎች” እጥረት የኢትዮጵያዉያን ውሎ በፌስቡክን ከፊል ደመናማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡በጨቋኞች የተከለከልነው ብሔራዊ እርቅ እና ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር ወይም የበኩላችንን ድርሻ ለመወጣት የግድ ሊቅ መሆን አይጠበቅብንም፡፡በግብጽ አስራ አብድልፈታህ የተባለች የ27 ዓመት ወጣት ናት የፈስቡክ ግሩፕ አቋቁማ ለአብዮቱ መነቃቃት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከት የቻለችው፡፡
ፌስቡክ እና መሰሎቹ የማሕበራዊ ትይይዝቶች ከሌሎች መካነ ድሮች በተለየ ብዙ ጥቅሞችን ይሰጣሉ፡፡ የመጀመሪያው በከፊል ወይም ሙሉ በሙሉ ለህዝብ እና ለአህዛብ ክፍት የሆነ ውስን ገጸ ርዕይ (profile) መክፈት ማስቻሉ ነው፡፡በዚህም መሰረት ከልጅነት እስከ እውቀት የሄድንበት መንገድ ፣ ከፊደል ቆጠራ እስከ ከፍተኛ ትምህርት የገበየንባቸው ተቋማት፣ ተቀጥረን የሰራንበት መስሪያ ቤት ፣ ከሀይማኖት እሰከ ቦለቲካዊ አቋማችንን የምናሰፍርበት በአጭር ጽሑፍ እና ምስል አስደግፈን ማቅረብ የምንችልበት ምህዳር አላቸው፡፡ ሁለተኛው ከሌሎች ተጠቃሚዎች ጋር የሚያገናኛቸው ትይይዝት መፍጠር መቻላቸው ነው፡፡ጓደኛና ወዳጅ በፌስቡክ በሽ በሽ ናቸው፡፡ ጊዜ ና ቦታ ሳይግደን የልብ የልባችንን ማዉጋት እንችላለን፡፡ከሌሎች መካነ ድሮች ያገኘናቸውን መረጃዎች(text, image and video) ለወዳጆቻችን በቀላሉ ማጋራት እንችላለን፡፡እነርሱስ ምን ሊግሩን ፈልገዋል የሚለውን ከገጻቸው ማግኘታችን ደግሞ ሰናይ ነው፡፡አይተን ብቻ አናበቃም፤ ወድጄዋለው (like) ከማለት በዘለለ በጉዳዩ ላይ አስተያየት መስጠት መቻላችን ከሌሎች ሰዎችም እሺ እንዴት አየኸው ብለንም መጠየቃችን ተወዳጅ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
ፌስቡክ እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ሀገሮች ቅንጦት አይደለም፡፡ማንኛውም ሰው ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሀሳብን የመግለጽ ነፃነት አለው የሚል ልፈፋን ለረጅም ጊዜ ብናደምጥም እውነታው ከዚህ የተለየ ነው፡፡ሌላው ቢቀር በቅርቡ በሽብርተኝነት የተከሰሱት ባረጀ ታፔላ ላይ በቃ!!! የሚል ጽሑፍ ልትጽፉ ወይም ልታጽፉ ስትመክሩ ተገኛችሁ በሚል ነው፡፡ የሚገርመው ህግን ለአመታት በከፍተኛ ተቋማት ያጠኑ ሰዎች ይህንን ለማውጣጣት የምስክር ጋጋታን ሲያደምጡ መክረማቸው ነው፡፡በማርያም!!! አሁን ይሄ በሽብርተኝነት ሊያሰከስስ ቀርቶ ግማሽ ቀን ወህኒ ያውላል?
በእንዲህ ያለ አይን ያወጣ ሽበባ ውስጥ በመኖራችን ነው ፌስቡክን እና ሌሎች መሰል ማኀበራዊ መካነ ድሮችን የሙጢኝ ማለት ያሰፈለገን፡፡ሌሎቹ መንገዶች ብዙም ላያዛልቁን እንደማይችሉ የሚዲያዎቻችንን ጥንካሬ እና ብስለት መመልከቱ ወደ ተስፋ መቁረጥ ይመራናል፡፡ አሁን አረጁ አፈጁ የሚባሉትን ሚዲያዎች ትተን እንደማሳያ የጡመራን(blogging) ብናነሳ ቀድሞ የተገነባ ጭፍን ደጋፊ (blind supporter) እና አሻሚ ፣ አደናጋሪ ስምን (fuzzy cult) ይጠይቃሉ ፡፡ በዚህም ምክንያት ከህዝባዊነት ይልቅ ቀድሞ የተገነባ የግለሰቦች ማንነት ሀሳብን ያንጸባርቃሉ፡፡የሚያካፍሉን ሀሳብ ከጀርባ ሌላ አጀንዳን እንዳላዘለ ማረጋገጥ ይከብደናል፡፡
ከታሪክ እንደተማርነው በየአዝማናቱ የነበሩ ክስተቶችን የተወሰኑ ሰዎች ወደፈለጉት አቅጣጫ ይመሯቸዋል(ለእኩይ ወይም በጎ ሊሆን ይችላል) በዚህም ምክንያት ወደድንም ጠላንም በሰው ዘር ላይ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፋቸው የማይቀር ነው፡፡ ይህንን የዘመን ጎርፍ ገድቦ ማስቀረት አይቻልም፡፡ ይልቅ የሚበጀው ወገብን ጠበቅ አድርጎ በወግ በወጉ ለሰናይ ምግባራት እንዲውል መግራት ነው፡፡ፌስቡክም ይህንን እየጠየቀን ነው፡፡እኔ የተመለከተኳቸውን ጥቂት ነጥቦች በማንሳት ላብቃ፡፡
የመጀመሪያው በገሀዱ አለም ያለው ማንነታቸችን እና በኢንተርኔቱ ዓለም የገነባነው ማንነት (cyber identity) ወደአሀድነት እያመሩ ነው፡፡ ስለዚህ በፌስቡክ እና ሌሎች መሰል ማኀበራዊ ትይይዝቶች ላይ ያለን እንቅስቃሴ እስኪገባን ድረስ ቁጥብ ፣ በኃላ ደግሞ ጥንቃቄን ከብስለት ጋር አጣምሮ የያዘ መሆን ይገባዋል፡፡የመካነ ድሮቹ ባለንብረቶችም ተኝተው አያድሩም፡፡ የግለሰቦችን ግላዊ ኑሮ እና ፍላጎት ላለመጋፋት የተለያዩ ስልቶችን ይቀይሳሉ፡፡(account and privacy setting)እነዚህን ለመረዳት ማስተዋል ፣ የተሻለ ተጋላጭነት(exposure) ያላቸውን ሰዎች ማማከር፣ ሰዎች ሲያዩኝ እንዴት ነኝ ማለት ያስፈልጋል፡፡(view as… in facebook) በመቀጠል ከሳይበር ወዳጆቻችን ጋር ያለን ግንኙነት በበኩሌ ኢትዮጲያዊ ጨዋነትን የተላበሰ ቢሆን እመርጣለው፡፡ይህንን ተፋልሶ በአዲስ ጉዳይ መጽሔት በሰፊው ያገኙታልና መድገም አያስፈልግም፡፡ መተዋወቁ፣ መወያየቱ እና በጋራ የምንወዳቸውን ነገሮች መለዋወጡን በክፉ ማየትን እቃወማለው፡፡ ከዚህ ያለፈ ወዳጅነት ካሻን ግን ነገሩን ከአየር ወደመሬት አውርደን እንደ ባለአእመሮ መነጋገር መልካም ነው፡፡
ሌላው ምክክር የሚያሻው ጉዳይ በዚህ አገዛዝ ላይ ያለን ቅዋሜ (antipathy to the regime)ነው፡፡ እርግጥ ነው ብዙዎቻችን የሀገራችን ችግር እና ችጋር አንገሽግሾናል፡፡በዚህም ከ facebook status update አንስቶ በተለያየ መንገድ ለሀገራችን መቸገር የአንበሳውን ድርሻ የሚይዘው የአቶ መለስ አስተዳደርን በቃህ እያልን ነው፡፡ ሰናይ ነው፡፡ እንደኔ ግን በጭፍኑ በቃህ ብሎ የቁራ ጩኸት ማሰማት መፍትሔ አይመሰለኝም፡፡ ብሔራዊ እርቅ እና ሀገራዊ መግባባትን ለማምጣት ቀድመው የበሰሉ እና የበለጸጉ የሳይንስ እና ፍልስፍና መርሖችን ከሀገራችን ሀይማኖቶች እንዲል (saying) ጋር በማቆራኘት ምን ይሻለናልን መጮህ፣ መስራት ይገባናል፡፡የሰው ልጆች የምድሪቱን ፍሬ በፍትህአዊነት ተካፍለው በፍቅር በሰላም በበጎ ሁኔታ እንዴት መኖር አለባቸው የሚለውን ለዘመናት የተካሄደ ተዋስኦ(discourse) በልካችን መስፋቱ የሚቀድም ይመስለኛል፡፡ እኔ “ሰውየው ምሁር ነው! ከእርሱ በላይ ሊቅ ከየት ሊመጣ? ተቃዋሚዎችን ተመልከቷቸው እርስ በርስ እንዴት እንደሚናከሱ!!!” ከሚሉት ወገን አይደለሁም፡፡ እርሱ ሀገሪቱን ቁልቁል የኋሊት እንደነዳት ማንም ይህን ማድረግ አያቅተውም፡፡ በፌስቡክ 440,080 ያህል ኢትዮጵያውያን ይገኛሉ፡፡ ቢያንስ እኛ እንኳን በመሰረታዊ የመጪው ጊዜ ጉዳዮች ላይ መግባባት ይጠበቅብናል፡፡
እውነተኛ ለውጥ፣ የማይቀለበስ ሰላም Facebook revolution, Twitter revolution, Revolution 2.0 በማለት፣ ይህን ደጋግሞ በማዜም፣ ስምን ደብቆ(by being anonymous) እንታገል፣ ቁረጠው፣ ፍለጠው በማለት አይመጣም፡፡ፌስቡክ አብዮት አዳዲሰ የፈጠራ መታገያ ስልቶችን፣ ራስን መቆጣጠርን እና ስነ ምግባርን ይጠይቃል፡፡ በመገ’ለጥ ሀሳብን ደግሞ ተንትኖ በመግለጥ እንጂ ተደብቆ ተራ ስድብን በመደርደር አይገኝም፡፡ የረጅም ጊዜ ውጤታማ ለውጥ እኛ ፌስቡክ ላይ ስለለጠፍን ሁሉን ነገር twit ስላደረግን አይመጣም፡፡የምንሰጠው መረጃ ይህን ለውጥ ፈላጊ ሀይል የሚያበረታ፣ የሚያጀግን ፣ የሚያነቃቃ፣ ልብን ስለፍትህ፣ ስለሰላም ፣ስለእኩልነት ፣ እንድትቃትት የሚያደርግ መሆን አለበት፡፡
ሌላው መታሰብ ያለበት ማኀበረሰባዊ ሚዲያ (social media) ቢሮ የለውም፡፡ ሉአላዊነት እንዲሁ፡፡ ይህ ደግሞ የሚጠቀማቸውን ነገሮች ነፃ ራሳቸውን የቻሉ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡በዚህም ምክንያት ትግሉ የሚካሄድበት ምህዳር በሌሎች ቁጥጥር ስር ነው፡፡እነዚህ ተቃውሞ መሳሪያዎች (facebook, twitter and other social Medias) በቀላሉ ወደ መጨቆኛ መሳሪያነት ተለውጠው ለድካም የፈጠረኝ ብነግድ አይተርፈኝ እንዳንል እስጋለው፡፡ኢንተርኔት አለአግባብ ጥቅም ላይ ሊውል፣ ለሳንሱር ሊጋለጥ ወይንም ሙሉ በሙሉ ሊዘጋ የሚችል ነገር ነው፡፡ በግብጽ አብዮት ኢንተርኔቱ ቢዘጋባቸው በአጭር የጽሑፍ መልዕክት እና የሬድዮ መገናኛ በመጠቀም ሙባረክን ከስልጣን ማውረዱን ከዳር አድርሰዋል፡፡ቻይና በቢሊዮን የሚቆጠር ሕዘብ ይዛ 527,720 ብቻ ፌስቡክ ተጠቃሚ(ከዓለም 93ኛ) ያላት ስለተዘጋነው፡፡የእንግሊዝ መንግስት የስራ አጥ ወጣቶችን አመጽ ለማፈን ፌስቡክን እንደሚዘጋ የዛተው በቅርብ ጊዜ ነው፡፡የአሜሪካ ኮንግረስአዲስ የሳይበር ህግ ሊያወጣ መሆኑን የሰሙ በርካታ መካነ ድሮች በቀዳሚ ገጻቸው ተቃዉሟቸውን ከገለጹ የጥቂት ቀናት እድሜ ብቻ አለፋቸው፡፡አሁን ብዙ መካነ ድሮችን ከእናት ሀገር ሆኖ በቀጥታ ማየት አይቻልም፡፡በብሎግ ስፖት የታገዙት ሁሉም ጦማሮች ሰሞኑን ወደወገኖቻቸው (ወደታፈኑት) ሳይቀላቀሉ አልቀረም ፡፡ ፌስቡክን መዝጋት ለሽመልስ ከማል(shameless camel) እኛ የቤታችንን መብራት እንደምናጠፋው የቀለለ ነው፡፡ ከዚያ የአለቃውን “ETV in Print” or “The Bereket Delusion” or“Berkleaks” or “Bereket and the Forty Thievesን ይዘን በቃላችን ማጥናት ነው፡፡ እስከዚያው ግን በአስተሳሰብ እንመንደግ ወርቃማው እድላችንን ፌስቡክን ትተን በፌዝቡክ አንጃጃል፡፡ ጄን ሻርፕ በብዙ ስራዎቹ አበክሮ እንደሚገልጸው አገዛዝ ጸንቶ የሚኖረው ባለው ሀይል፣ ነፍጥ እና ጭቆናው ሳይሆን በህዝቦች ለመጨ’ቆን በተዘጋጀ ልብ እና ፈቃድ ነው፡፡ወደሽ ከተዳፋሽ ቢረግጡሽ አይክፋሽ እንዲል የኛ ሰው፡፡ please Log out from ‘fazebook’ but log in to facebook